መስከረም 23 ፤ 2017

የኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለ አደራ ድርጅት ከመቅደላ ጦርነት የተዘረፈው የ19ኛ ክፍለ ዘመን ጋሻእንዲመለስ ስኬታማ ድርድር አደረገ

ባህላዊ ቅርሱ ለአጭር ጊዜ በToledo Museum of Art ለትይንት ከቀረበ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳል

የኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለ አደራ ድርጅት፣ በዛሬው ዕለት ፣ እ.አ.አ. ጥቅምት 3, 2024 ዓ.ም. የመቅደላን ጦርነት ተከትሎ በአስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን በእንግሊዝ ወታደሮች የተወሰደውን ጋሻ ለሕዝባችን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ የተሳካ ድርድር ማድረጉን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለ አደራ ድርጅት፣ የኢትዮጵያን ዘውድ ትዉፊትና ታሪክ ለማስቀጠል፣ የኢትዮጵያዊያንን ባህል ለማስታዋወቅና የኢትዮጵያንም ሕዝብ በትምህርትና በኤኮኖሚ ለማበልጸግ በቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ የልጅ ልጅ፣ በልዑል ኤርሚያስ ሣኅለ ሥላሴ የተቋቋመ ትርፍ አልባ ድርጅት ነው።

እ.አ.አ. በ1868 ዓ.ም. ከመቅደላ ጦርነት በኋላ ተዘርፈው ከተወሰዱ በርካታ የሃገራችን ቅርሶች ጋሻው አንዱ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለ አደራ ድርጅት በእንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው የAnderson & Garland አጫራች ኩባንያ ጋር ተደራድሮ ወደ አትዮጵያ እንዲመለስ በተሳካ ሁኔታ ከስምምነት መድረሱ ጥልቅ ታሪካዊ ሚናና ባህላዊ ትርጉም አለው። ባለፈው የካቲት ወር ጨረታ ላይ ሊውል የነበረው የመቅደላ ጋሻ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ባቀረበው የይገባኛል ጥያቄ መሰረት እንዲነሳ ከተደረገ በኋላ፣ በልዑል ኤርሚያስ ሣኅለ ሥላሴ መሪነት፣ የኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለ አደራ ድርጅት፣ የተቋቋመበትን ዓላማ መመርያ በማድረግ፣ የተዘረፈው ጋሻ ወደ አትዮጵያ በክብር እንዲመለስ ስኬታማ ድርድር ለማድረግ ችሏል።

“ይህ ጋሻ ታሪካዊ ቅርስ ብቻ አይደለም፤ የኢትዮጵያ የብዙ ሺ ዘመናት ታሪክ ነፀብራቅ፣ የሕዝባችንን አትንኩኝ ባይነትና ጥቃት የመቋቋምና የመከላከል ብቃቱ ማሳያና ምልክትም ጭምር ነው” ብለዋል ልዑል ኤርሚያስ ሣኅለ ሥላሴ። “የኛ የተሳካ ድካምና ልፋት ላለፉት 156 ዓመታት ከኢትዮጵያ ተሰውሮ የነበረው የመቅደላ ጋሻ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ለማስማማት መቻላችን፣ የሀገራችንን ውርስና ቅርስ ለማስጠበቅ፣ የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለማስከበርና ለምንወዳት ሀገራችን መስዋዕት የከፈሉ አባቶቻችንን ለማክበርና ታሪካቸውን ለመዘከር ያለንን ቁርጠኝነት ይመስክራል” ሲሉም ልዑልነታቸው አክለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለአደራ ድርጅት
የማግዳላ ጋሻ
የኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለአደራ ድርጅት
የንጉሠ ነገሥቱ ልዑል ኤርሚያስ ሳህለ-ሥላሴ ኃይለ ሥላሴ ወደ ኢትዮጵያ ከሚመለሱት መቅደላ ጋሻ ጋር ቆመው

እ.አ.አ. በ1868 ዓ.ም. በእንግሊዝና ኢትዮጵያ መካከል የተደረገው ጦርነት የኢትዮጵያን ሕዝብ ብዙ ዋጋ አስከፍሏል። የአጼ ቴዎድሮስ የመጨረሻ ምሽጋቸው የነበረው መቅደላ፣ በእንግሊዝ መንግሥታት ወታደሮች ከተያዘ በኋላ የአጼዎቹን ዘውዶች፣ የቤተ ክህነታችን ጽላት፣ ጽዋና መስቀሎች፣ የቤተ መንግሥት አልባሳት፣ የጦር መሳርያዎችና በርካታ የሀገር ቅርስች በእንግሊዝ ወታደሮች ተዘርፈዋል።

ከላይ የተጠቀሰውን ጋሻ ለማስመለስ የኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለ አደራ ድርጅት ከዶ/ር አሉላ ፓንክኸርስት ጋር አብሮ ሰርቷል። ዶ/ር አሉላ ፓንክኸርስት፣ ኢትዮጵያን ከፋሽስት ኢጣልያን ነጻ ለማውጣት የታገሉት የSylvia Pankhurst የልጅ ልጅ እንዲሁም ቅርስ በማስመለስና የኢትዮጵያን ታሪክ በረቂቅ አዋቂ የነበሩ የፕሮፈሰር Richard Pankhurst ልጅም ናቸው።

“ይህንን ባህላዊ ቅርስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለማስረከብ ከልዑል ኤርሚያስና ከኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለ አደራ ድርጅት ጋር ለመስራት በመቻሌ ከፍተኛ ክብር ተሰምቶኛል” ብለዋል ዶ/ር አሉላ ፓንክኸርስት። “ቤተሰቦቻችን ለብዙ ዘመናት የኢትዮጵያዊያን ዉርስና ቅርስ በክብር እንዲጠበቅ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ብዙ ለፍተዋል። በእጃችን ያስገባነው ጋሻ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መልሰን ለማስረከብ ከስምምነት መድረሳችን በቤተሰቦቻችን የተጀመረው ቅርስ የማስመለስ አኩሪ ታሪክ በኛ እንደቀጠለ ጥሩ ማሳያ ነው” ብለው ዶ/ር አሉላ አክለውም ገልጸዋል።

እ.አ.አ. ከጥቅምት 1 እስከ ጥቅምት 27, 2024 ዓ.ም. ጋሻው ወደ ኢትዮጵያ ከመመለሱ በፊት፣ በልዩ ሁኔታ “Ethiopia at the Crossroads” በተሰኘው ኤግዚቢሽን፣ በToledo Museum of Art ለትይንት ይቀርባል። ከዚያ በኋላ፣ ጋሻው በህዳር ወደ ኢትዮጵያ በክብር ከተመለሰ በኋላ፣ በብሔራዊ ሙዚያም ለሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብና ለተቀረው ጎብኚ የዓለም ሕዝቦች እይታ በክብር እንደሚቀመጥ ተገልጿል።

ስለ ኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለ አደራ ድርጅት

የኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለ አደራ ድርጅት፣ የኢትዮጵያን ዘውድ ትዉፊትና ታሪክ ለማስቀጠል፣ የኢትዮጵያዊያንን ባህል ለማስታዋወቅና የኢትዮጵያንም ሕዝብ በትምህርትና በኤኮኖሚ ለማበልጸግ በልዑል ኤርሚያስ ሣኅለ ሥላሴ የተቋቋመ ትርፍ አልባ ድርጅት ነው።

የኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለ አደራ ድርጅት፣ አራት ዋናና መሰረታዊ አላማዎች ወይም የስራ መስኮች አሉት። በዋናነት የኢትዮጵያን ታሪክና ባህላዊ ቅርሶች በክብር እንዲጠበቁ ለማድረግ ሲሆን፣ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ወጣቶች የተሻለ ዕድል እንዲኖራቸው በትምህርት ማበልጸግ፣ በልዩ ልዩ የንግድና የፈጠራ ስራ ላይ ሕዝባችን ተሳታፊ እንዲሆን በሮችን በመክፈት ድጋፍ ማድረግ እንዲሁም የአትዮጵያ ዘውድ የአንድነታችን ምልክትና አርማ ሆኖ እንዲቀጥል ባህላችንን፣ ውርስና ቅርሶቻችንን በክብር ለማቆየትና ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ እንዲቻል በሁለንትናዊ መልኩ ለኢትዮጵያ ዘውድ ድጋፍ ማድረግ የኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለ አደራ ድርጅት ቀዳሚ አላማዎች ናቸው።

ስለ መቅደላው ጋሻ

የመቅደላው ጋሻ ወይም የኢትዮጵያ ጋሻ በመባል የሚታወቀው ሀገራዊና ባህላዊ ቅርስ እ.አ.አ. በ1868 ዓ.ም. በመቅደላው ጦርነት ጊዜ በእንግሊዝ ወታደሮች ተዘርፎ ነበር። የመቅደላ ጦርነት የተካሄደው የእንግሊዝ መንግሥት ወታደሮቿን ወደ ኢትዮጵያ ከላከቻቸው በኋላ ነው። አጼ ቴዎድሮስ በእንግሊዝ ወታደሮች መከበባቸውን ሲያውቁ፣ እጄን አልሰጥም በማለት፣ የያዙትን መሳርያ በራሳቸው ላይ አዙረው፣ ቃታውን በመሳብ፣ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ተደፍሮ በህይወት እያሉ ከሚያዩ ለዘውድ ክብርና ለሀገር ፍቅር ሲባል መሰዋትን የመረጡበት ታላቅ ጦርነት ነበር። ከጦርነቱ በኋላ የእንግሊዝ ወታደሮች የአጼ ቴዎድሮስን ያጌጠን ጋሻ ጨምሮ ሌሎችም በርካታ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶቻችንን ዘርፈው ወደ ሀገራቸው ወስደውታል።

የኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለ አደራ ድርጅት ያስመለሰው ቅርስ በልዩ ባህላዊ ጥበብ ከብረት የተሰራ፣ ዙርያው ቆዳና በብር ማዕድን ያጌጠ ጋሻ ነው። የመቅደላን ጦርነት ታሳቢ ለማድረግ ጦርነቱ የተካሄደበትን ዕለት በማስታወስ “ሚያዝያ 13, 1868” የሚል ጽሁፍ ተቀርጾበታል። ይህንን ጋሻ ከተዘረፈ ከመቶ ዓምሳ ስድስት ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለ አደራ ድርጅት እንዲመለስ የተሳካ ድርድር ቢያደርግም፣ እስከዛሬ ድረስ ያልተመለሱና የወደሙትን ሌሎች በርካታ ባህላዊ ቅርሶቻችንን እንዲሁም ያጣነውን ታሪካዊ ሀብትና ባህላዊ እሴቶችን ሁሉ ዘወትር እንድናስባቸውና በመጨረሻም ለሀገርና ለወገን እንድናበቃቸው ሊያበረታታን ይገባል። ይህን ጋሻና ሌሎች የተዘረፉን መሰል ቅርሶች እንዲመለሱ ለማድረግ ለበርካታ ዓመታት ካለማቋረጥ ብዙ ተለፍቶበታል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በርከት ያሉ ቅርሶች፣ የመቅደላውን ጋሻ ጨምሮ፣ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ተቃውሞና ጥያቄ አማክኝነት ከተለያዩ ጨረታዎች እንዲወርዱና አንዳንዶቹም ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ሆኗል።

ሕዝብ ግንኙነት  |  ልጅ ነብያት አክሊሉ  |  (330) 310-6749   |  ndemessie@gmail.com

ቤተሰባችን ይቀላቀሉ

ልዩ ግንዛቤዎችን እና ዝመናዎችን ለማግኘት ለጋዜጣችን ይመዝገቡ

A Legacy Restored - The Return of the Shield of Magdala