መስከረም 3, 2025
የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሞቱበት 50ኛ ዓመት መታሰቢያ
ንጉሠ ነገሥቱ ከውልደት እስከ ሕልፈተ ሕይወት ዕንቆቅልሽ ሆነው ቆይተዋል። በሁለት ዓለማት መካከል ተወጥረው ተይዘው ነበር። አንዱ በጣም ጥንታዊ በባሕሉ እና ልማዱ የሚኮራ፤ ሌላኛው ከሃያኛው ክፍለ ዘመን ጋር ለመድረስ በጥድፊያ የተመላ።
ለዘመናት ከዓለም ተነጠላ የቆየችው ኢትዮጵያ፤ የመካከለኛው ዘመን ውርሰ አሻራ መሰናክሎች ቢኖሩም ሀገረ መንግሥት ለማቆም በሂደት ላይ፤ የውስጥ እና የውጭ ስጋቶች ተደቅነውባትም ሳለ ሉዓላዊነቷን ለመፍጠር እና ለማስጠበቅ ትግል ላይ ነበረች።
እነዚህን የማይታረቁ የሚመስሉ ፈተናዎችን በመጋፈጥ ንጉሠ ነገሥቱ በእምነት፣ በዲሲፕሊን እና በፅናት በመታገል ለሀገራቸው ዘመናዊነትን ለማምጣት ጥረት አድርገዋል፤ አፍሪካን ከቅኝ ግዛት ባርነት ነፃ ለማውጣት ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል።
ገና ጨቅላ ሳሉ እናታቸውን፤ በአሥራ ሶስት ዓመታቸውም አባታቸውን በማጣቸው ከልጅነታቸው አንስቶ ብርቱ ሐዘን ገብቷቸዋል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መዳረሻ እ.ኤ.አ. በ1936 ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት የቀውስ ወቅት ሙሉ በሙሉ ተገልለዋል፣ ሀገራቸውን እንዲለቅቁም አሳልፈው ተሰጥተዋል።
እኒህ ተግዳሮቶች በሰብዓዊነት ላይ ያላቸውን እምነት ፈትነዋል፤ የዓለም አቀፍ ፖለቲካን ግብዝነትም አስተምሯቸዋል። ሆኖም ለሕዝባቸው ፍትሕን ከመፈለግ አልገቷቸውም፤ ይህም በዓለም ዙሪያ ካሉ ነፃነት ወዳዶች ዘንድ አድናቆትን አትርፎላቸዋል።
የንጉሠ ነገሥቱ ተቺዎች በስደት ምቾት እና ደህንነትን ፍለጋ ሀገራቸውን ጥለው እንደ ሄዱ አድርገው ከሰዋቸዋል። ሆኖም፤ በእኒያ አዋኪ ዓመታት ውስጥ የከወኗቸውን ያላሰለሱ ሥራዎች እውነታ አንፀባራቂ አይደሉም።
ንጉሠ ነገሥቱ ምንም አንኳ ዙፋናቸውን ቢያጡም እና ከፋሺስቶች አሳፋሪ ጥቃት ቢሰነዘርባቸውም፤ ሁሌም ክብራቸውን ጠብቀው ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሠርተዋል። ብልህ የፖለቲካ እና የአመራር ብቃታቸውን ተጠቅመው ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ነፃ አውጥተዋል። ስደት ሸክም፣ እጦት እና ብቸኝነት ቢኖረውም እኒያን የጭቆና ዓመታት ተወጥተው ስለ መጪዎቹ ጊዜያት ለማሰላሰል ተጠቅመውበታል።
ሀገራቸውን ከጋራ ሥነ ልቦናዊና የውስጣዊ ስሜት ጉዳት አገግማ እንድትነሳ የማድረግ እና ሕዝባቸውም ወደፊት ለሚጠብቀው የመልሶ ግንባታ ሥራ ተስፋን ማላበስ ነበረባቸው። የንጉሠ ነገሥቱ ጠላቶቻቸውን ያለመበቀል እርምጃ ከሕዝባቸው እና ዓለም አቀፍ መሪዎች መሪዎች ዘንድ አድናቆትን አስገኝቶላቸዋል።
ንጉሠ ነገሥቱ በታላቅ ብርታትና ርዕይ ዳግም ሀገራቸውን መገንባት ጀመሩ። ለትምህርት ትኩረት በመስጠት የኢትዮጵያን ልማት የሚመራና የሚረዳ የተማረ ክፍል መገንባት ያዙ። በግብርና፣ በትምህርት እና በኢንዱስትሪ ማስፋፋት ትልቅ እመርታ አሳዩ። ዘመናዊ የምድር ጦር፣ አየር ኃይል እና ባሕር ኃይል መገንባት ቻሉ። እነዚህ አስደናቂ ድሎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ዘመናዊነትን ወደ ለሀገራችን የማስገኘት ስኬታቸው ግና በመከፋፈል እና የውስጥ ግጭቶች ተፈትኗል፣ ያም ኢትዮጵያን ለዘመናት አውኳል።
የኋለኛው የግዛት ዘመን ከፍተኛ ውጤትን በመጠበቅ የተፈተነ ነበር። ተከታዮቹ ዓመታትም የተገንጣዮች እንቅስቃሴዎች፣የተማሪዎች ንቅናቄዎች እና የቢሮክራሲው ፍላጎቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ የመጡባቸው ነበሩ። ንጉሠ ነገሥቱ ውሎ አድሮ እርሳቸውን ከስልጣን የሚያወርዱ እና ሀገሪቱን የማይታወቅ መከራና ሽብር ውስጥ የሚከቱ የለውጥ ጥያቄዎችን ቀደም ብለው መገንዘብ ተስኗቸው ነበር። የእርስ በእርስ ጦርነት፣ ሽብር እና ረሃብ የሀገሪቱ መለያዎችና ወደ ገደል የሚያወርዱ ሆነዋል።
እኒያ ዓመታት በእጅጉ የከፉ ጉዳቶችን አስከትለዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለለውጥ፣ ፈጣን የዴሞክራሲ እና የምጣኔ ሃብት ልማት ጉዞ መሻትን አሳይቷል። በምትኩ፤ የሥርዓተ-አልበኝነት እና ለዘመናት የተገነባ ባሕል መናድ ታጋች ሆኖ ቆይቷል፤ ለተወሳሰቡ ችግሮች እና ፈተናዎች የቀረበው ብቸኛ መፍትሔም ገደብ የለሽ ኃይል ነበር።
ከብሩሁ ንጉሠ ነገሥታችን ሕልፈተ ሕይወት አንስቶ ያለፈውን ግማሽ ክፍለ ዘመን በምልሰት ስናነሳ በእጅጉ መስዋዕትነት በከፈሉ፤ ከቶውንም ኢትዮጵያን ወደ ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ያሻግራሉ ብለው ተስፋ ባሳደሩባቸው እኒያው ሰዎች መገለልና መገደል ደርሶባቸዋል።
ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ በሕግ፣ በውክልናና በተጠያቂነት ላይ የተመሠረተ ሥርዓት መፍጠር ተስኖናል። ከታሪካችን ጋር መታረቅ ተስኖናል። ለሕዝባችንና ለሀገራችን የመረጋጋት ርዕይ መቅረፅ ተስኖናል፤ ኢትዮጵያ በሙሉ ልብ ወደፊት አሻግራ እንድታይ የሚያስችል ርዕይ እነሆን ማለት ተስኖናል።
ያለፉትን ሃምሳ አመታት መለስ ብለን ስናስብ እና የንጉሠ ነገሥቱን ሕይወት እና ውርሰ አሻራ ስንመረምር ንጉሠ ነገሥቱም ሰው መሆናቸውን ልብ እንላለን። ሕይወታችውን ሙሉ የተፈተኑ እና አያሌ የግል አሳዛኝ ሁኔታዎችን የተወጡ ነበሩ። ርዕሰ ብሔር እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበላይ ጠባቂ በመሆን ከፍተኛ ኃላፊነትን ተሸክመዋል።
ሀገራቸው ስትከዳ የዓይን እማኝ የሆኑ ሰማዕት ነበሩ፤ የቤተሰብ አባሎቻቸው እና ሀገሪቱን እንዲመሩ ያበቋቸው ሰዎች ሲገደሉ ተመልክተዋል። እንዲያም ሆኖ፤ እስካሁንም ድረስ እንደ ሀገር ወዳድነታቸው እና ዓለም አቀፍ መሪነታቸው የሚመጥናቸው ዕውቅና አላገኙም።
ይህን ለማድረግ ሙሉ አቅም እያላቸው ግና የራሳቸውን ሕዝብ ደም ለማፍሰስ እምቢኝ ያሉ፣ አብነት የሆኑ፣ ጥልቅ እምነት የነበራቸውና አርቆ አስተዋይ መሪ ነበሩ። የንጉሠ ነገሥቱን ስም እና ውርሰ አሻራዎች ለማጉደፍ ብዙ ትችቶች እና ጥረቶች ቢደረጉም በመጪው ትውልድ ዘንድ ግና አያሌ ስኬቶቻቸው አድናቆትን ይቸራሉ።
ኢፍትሐዊነትን ለመዋጋት፣ አፍሪካን ነፃ ለማውጣት እና የአፍሪካውያንን ድምፅ በዓለም መድረክ የማሰማት ሥራቸው በታሪክ ውስጥ ተቀርጿል። ለተጨቆኑ ሰዎች ተስፋን አጎናፅፈዋል። በዓለም ዙሪያ የጥቁር ኩራት ምልክት ሆነዋል። በአፍሪካ አንድነት ድርጅት አማካኝነት የመላው አኅጉር አባት ለመሆን በቅተዋል፤ በራስ ተፈሪያን አማካኝነት ሉላዊ የጥቁር የነፃነት ንቅናቄ መንፈስን አነሳስተዋል።
የልጅ ልጁ እንደመሆኔ፣ በትምህርታችን ላይ እንድንተጋ ያበረታቱን እንደነበር አስታውሳለሁ። ስለ ቤተሰባችን፣ ግዴታችንና ሀገራችን አስተምረውናል።
ለመጪዎቹ በርካታ ዓመታት በጉጉት ሕይወታቸውን ለመዘከር እና ለማክበር እንጠባበቃለን።.
እግዚአብሔር ሕይወታቸውን እና መታሰቢያቸውን ይባርክ።
