የኢትዮጵያ ታሪክ

የኢትዮጵያ ታሪክ

የኢትዮጵያ ታሪክ እና ባህል በዓለም ካሉት ታላላቅ ከሚባሉት ታሪክ እና ቅርፅ ካላቸው ሀገራት ውስጥ ይመደባል። በአርኪኦሎጂ ምርመራ የተገኙ ማስረጃዎች መሠረት ወደ ሦስት ሺህ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በታላላቅ ከተሞች እና መንደሮች መደራጀቷ ተረጋግጧል። ኢትዮጵያ ከግብፅ እና ኑቢያ ጋር በአፍሪካ ውስጥ ካሉት ጥንታዊ ታሪካቸውን በጽሑፍ ካስቀመጡ ጥቂት አገሮች አንዷ ናት።   ጥንታዊ መንግሥቷን በሰሜን ግዛት አክሱም ላይ መሥርታ በአካባቢው ከነበሩት ታላቅ መንግሥት ሆና ከጥንታዊ የሮማዊያን እና የደቡብ እስያ (ህንድ) ኃያላን መንግሥታት ጋር በንግድ እየተገናኘች ወታደራዊ ኃይሏን እና ግዛቷን በማንሰራፋት አሁን ሱዳንና የመን የሚባሉትን ታስተዳድራቸው ነበር።  የአክሱም ሐውልቶች ከአፍሪካ ታላላቅ ጥንታዊ ቅርጾች መካክል ይመደባሉ።

ምዕራባዊያን የ”ሚዲቫል” ዘመን ወይም የጨለማው ዘመን ብለው በሚጠሩት ወቅት ኢትዮጵያ የሚያኮራ ታላቅ የስነጽሑፍ እና ስነስዕል ጥበብ እያዳበረች ነበር።  ለዚህም ትልቅ አስተዋጾ ያበረከተችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት።በታላቁ ክብረ ነገሥት የንጉሥ ሰሎሞን እና የንግሥተ ሳባን ታሪክ ተጽፎ እናገኘዋለን።  በተጨማሪም ልጃቸው ቀዳማዊ ዓፄ ሚኒልክ ታቦተ ጽዮንን ወደ ኢትዮጵያ እንዴት አድርጎ እንዳመጣና የኢትዮጵያ የመጀመርያው ሰሎሞናዊ ንጉሠ ነገሥት ሆኖ እንደነገሠም ይነግረናል።

ዛሬ ኢትዮጵያ የነጻነት እና የፀረ ቅኝ ግዛት ተምሳሌት ናት። መላው የአፍሪካ አህጎር በቀኝ ገዢዎች ቀንብር ስር ሲወድቅ በዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በየካቲት ፳፫ ቀን ፲፰፻፹፰ ዓ.ም. ኢትዮጵያ የጣልያን ወረራን አሸንፋ ነፃነቷን አስከብራለች። በድጋሚ ከአርባ ዓመት በሗላ በሙሶሊኒ መሪነት ፋሽስት ጣልያን አገራችንን ሲወር ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ በጦር ሜዳም በዲፕሎማሲም ታላቅ ተጋድሎ አድርገዋል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ አፍሪካን ከቅኝ ግዛት ነፃ ለማውጣት በሚደረገው ትግል ዓለም አቀፍ ድምጽ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለአደራ ድርጅት

ኢትዮጵያ ከደርግ አብዮት ወዲህ

በ፲፱፻፷፯ ስልጣን የተቆጣጠሩት ኮምዩኒስት የጦር ሰራዊት አባላት አገሪቷን “ደርግ” በተሰኘ ወታደራዊ ኮሚቴ ያስተዳድሩ ነበር። ብዙም ሳይቆይ በመላ ኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ይስፋፋ ጀመር። በተጨማሪም እበ፲፱፻፸ዎቹ መጨረሽ ላይ በኢትዮጵያ ታይቶ የማይታወቅ ረሃብ ገብቶ አገሪቷን ከስቃይ ወደ ባሰ ሰቆቃ ውስጥ አስገባት። ጦርነቱም እያየለ ሄዶ ደርግ በ፲፱፻፹፫ ዓም የደርግ ምንግሥት ወድቆ የሕዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ (የትግራይ ሕዝባዊ ነጻ አውጪ ግንባር | ትሕነግ) የመንግሥት ስልጣን ጨበጠ።ኢትዮጵያን ብሔርን መሠረት በማድረግ አካሎ እስከ፳፻፲፫ ድረስ ግዝቷል።

Crown Council of Ethiopia

የኮሚኒስቱ ደርግ በ፲፱፻፷፯ ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለ ሥላሴን ከሥልጣን አውርዶ በ፲፱፻፷፰ የዘውዱን እንዲሁም የህይወታቸው ፍጻሜ አድርጎል። ልጃቸው ልዑል አልጋ ወራሽ መርዕድ አዝማችህ አስፋ ወሰን ኃይለ ሥላሴ በአብዮቱ ጊዜ ውጭ አገር በሕክምና ላይ ስለ ነበሩ በአገራቸው ውስጥ የተነሳውን የነውጥ ማእበል ለማቆም ወይም ለመቋቋም አልቻሉም። በ፲፱፻፹፩ በመጋቢት ወር በስደት ይኖሩባት በነበረችው ለንደን ከተማ አሳውጀው ቀዳማዊ አፄ አምሃ ሥላሴ ተብለው በስደት የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሆነው ተሰየሙ።

በዚያም መሠረት የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤትን እንደገና አዋቅረዋል። የዘውድ ምክር ቤቱ ኃላፊነት ንጉሠ ነገሥቱን ማማከር ሲሆን ዙፋኑ ተቀማጭ ንጉሥ በሌለበት ግዜ ዘውዱን በመወከልና ስርዓቱን በመጠብቅ ያገለግላል። በ፲፱፻፹፭ ዓም የወንድማቸውን ልጅ ልዑል ኤርሚያስ ሣህለ ሥላሴን የዘውድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አድርጎ ሾመዋል። በየካቲት ፲፱፻፹፱ ዓም ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ዓፄ አምሃ ሥላሴ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩበት ጊዜ ጀምሮ፣ ልዑል ኤርሚያስ ሣኅለ ሥላሴ በዘውድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንትነታቸው የኢትዮጵያን ዘውድ በመወከል  ሕገ መንግሥታዊ ንጉሣዊ ሥርዓት መልሶ እንዲጸና እና በመላ አገሪቱ በርካታ የበጎ አድራጎታዊ እና የባሕልና ታሪክን የሚደግፉ ስራዎችን በመደገፍ ይሰራሉ።

የኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለአደራ ድርጅት

የዘውዱ ምክር ቤት የህጋዊ ሚና

የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት በዙፋን ላይ ያሉትን ነገሥታት የሚመክር የሕገ መንግሥታዊ አካል ነው። ዙፋኑ ተቀማጭ ንጉሠ ነገሥት በሌለው ጊዜ ምክር ቤቱ የአገሪቱን ዘውድ ወክሎ ይሰራል። የምክር ቤቱ አባላት በንጉሠ ነግሥቱ ተሹመው በምክር ቤቱ ፕሬዘዳንት ስር ያገለግላሉ። ንጉሥ በሌለበት ወቅት የምክር ቤቱን አባላት የመሾም ሆነ የመሻር ስልጣን የፕሬዚዳንቱ የልዑልነታቸው ልዑል ኤርምያስ ሣህለ ሥላሴ ኃይለ ሥላሴ ሀላፊነት ነው።